12/11/2019
የደም ማነስ
'''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''
የደም ማነስ ምንድነው?
'''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''
አንድ ሰው የደም ማነስ ህመም አለበት የሚባለው በአንድ ወይም ከአንድ በላይ በሆኑ ምክንያቶች በደም ውስጥ የቀይ ደም ህዋሳት ቁጥር ሲመናመን ነው።የነዚህ ቀይ ደም ህዋሳት ተግባር በባለፈው ‘ቀዩ ቦርሳ’ በተሰኘው ጽሁፍ እንደተወሳው አየር መሸከም ሲሆን ቁጥራቸው በሚመናመንበት ጊዜ ከዚሁ ተግባር መስተጓጎል ጋር የተያያዘ ስሜቶችና (symptoms) ምልክቶች (signs) ይታያሉ።
ለመሆኑ እኒህ ስሜቶች ምን ምን ናቸው?
'''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''
ከፍተኛ የድካም ስሜት
ማዞር
ጆሮ ውስጥ ጭውው የሚል ድምጽ መሰማት
ብዥ ማለትና አንድ ነገር ሁለት መስሎ መታየት
የልብ ምት መሰማት እና የመሳሰሉት ሲሆኑ የደም ማነሱ የከፋ ሲሆን ደግሞ ትንፋሽ ማጠርና ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፣ የደረት ውጋትና የእግር ማበጥ ሊከሰት ይችላል። ይህም ልብ የደም እጥረቱን ለማካካስ በምታደርገው ከፍተኛ ትግል ከጊዜ በኋላ እየደከመች በምትሄድበት ወቅት የሚከሰት ሁኔታ ነው።
ሃኪሞች በሚመረምሩበት ወቅት ደግሞ የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያስተውሉ ይችላሉ።
የፊትና የአይን ቆብ ውስጠኛው ክፍል መገርጣት/መንጣት
የምላስ ልሙጥ መሆን ወይም ስጋ መምሰል
የአፍ ጠርዝና የከንፈር ቁስለት
የመዳፍና የውስጥ እግር መንጣት/መገርጣት እና ወዘተ ሲሆኑ በተጨማሪም ለደም ማነሱ መንስኤ የሆኑ ሌሎች የውስጥ ደዌ ምልክቶችም ሊታዩ ይችላሉ።
ስለምን እኒህ የቀይ ደም ህዋሳት ቁጥራቸው ይመናመናል?
'''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''
በአጠቃላይ የደም ማነስ ምክንያቶችን በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ማየት ይቻላል
1. ከሰውነት ደም መፍሰስ፣
በአደጋ፣
በወሊድ ጊዜ፣
የወር አበባ ከተለመደው ሲበዛ፣
በቀዶ ህክምና ወቅት
ከጨጓራና ከተለያዩ የውስጥ ኣንጀት ቁስሎችና እባጮች መድማትና ወዘተ
2. የቀይ ደም ህዋሳት ቁጥር ማነስ
-በበቂ ቁጥር ያለመመረት (የመቅኒ መስተጓጎል፣የብረት iron ቫይታሚን ቢ 12 እና ፎሊክ ኣሲድ እጥረት)
-የተፋጠነ የቀይ ደም ህዋሳት መሞት፣
በተለይም በሃገራችን ዋነኛው የደም ማነስ መንስኤ ከብረት (iron) እጥረት የሚመጣ ሲሆን ይህም የተመጣጠነ ምግብ ኣቅርቦት በቂ ባለመሆኑና በሆድ ውስጥ ደምን የሚመጡ ትላትሎች በብዙ የሃገራችን ማህበረሰብ ውስጥ በመኖራቸው ነው።
በብረትና(iron) በቫይታሚን (vitamin) እጥረት የሚከሰተው ደም ማነስ የትኛው የማህበረሰብ ክፍል ይበልጡን ተጋላጭ ነው?
'''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''''
-ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች
-ህጻናትና ታዳጊዎች፣
-ቲቢንና ኤች አይ ቪን ጨምሮ የተለያዩ ህመም ያለባቸው ወገኖች፣
-ስጋን ጨምሮ የተለያዩ የእንስሳት ተዋጽኦዎች በበቂ ሁኔታ ማግኘት የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብ እጥረት ወዘተ
እንዴት ይታወቃል?
,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,
ከላይ ያሉት ስሜቶችና ምልክቶች በብዙ ህመሞች ላይ የሚስተዋል በመሆኑ ታማሚው በኣቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ ሊያደርግ ይገባል።
የጤና ባለሞያዎችም የሚከተሉትን ምርመራዎች በላቦራቶሪ እንደየአስፈላጊነታቸው ሊያዙ ይችላሉ።እነዚህም ምርመራዎች የደም ማነስ መኖሩንና መንስኤውን ለማውቅ ይረዳሉ።
-ሙሉ የደም ቆጠራ፣ የቀይ ደም ህዋሳትን ብዛት ለማወቅ
-በማይክሮስኮፕ በመታገዝ የቀይ ደም ህዋሳት መልክና ቅርጽ ምርመራ፣
-የብረትና የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ፣ቫይታሚኖችን ጨምሮ መጠናቸውን ከደም ውስጥ መለካት፣
-በተመረጡ ሁኔታዎች ከአጥንት መቅኒ ናሙናም ሊወሰድ ይችላል።
እንዴት ይታከማል?
,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,
ህክምናው እንደየምክንያቶቹ የተለያየ ቢሆንም የከፋ የደም ማነስ ያለ እንደሆነ ግን ከህመምተኛው የደም አይነት ጋር ተስማሚ የሆነ በህክምና ተቋም ውስጥ ደም በመስጠት የታካሚውን ህይወት መታደግ ይችላል።ለመጠነኛና መካከለኛ የደም ማነስ ግን ለደም ማነሱ ምክንያት የሆነውን ነገር በመለየት ይታከማል።
በንጥረ ነገሮች እጥረት ለተከሰተ የደም ማነስ እጥረት ያለበትን ንጥረ ነገር በመስጠት ይታከማል።
-የብረት(iron) እጥረት ፣ በብረት የበለጸጉ እንክብሎችን በመስጠት (ferrous sulphate, ferrous fumarate, ferrous gluconate) እንዲሁም በፍጥነት ብረቱን መተካት ሲያስፈልግ በመርፌ የሚሰጥ የብረት ቅንብር( dextran) መስጠት ይቻላል።
-ለቫይታሚን ቢ 12 vitamin B 12 እጥረት ፣በመርፌ cobalamin የተሰኘ መድሃኒት ይሰጣል።
-ለፎሊክ ኣሲድ እጥረት የ folic acid እንክብል በመስጠት ይታከማል።
በሌሎች ምክንያቶች የሚመጡት እንደየምክንያቱ የሚታከሙ ይሆናል።
መከላከል ይቻል ይሆን?
,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,
ከላይ እንደጠቀስነው በሃገራችን ዋነኛው የደም ማነስ ምክንያት የንጥረ ነገሮች፣ በተለይም የብረት እጥረት እንደመሆኑ በብረትና በቫይታሚች የበለጸጉ ምግቦችን መመገብ በነዚህ ንጥረ ነገሮች እጥረት የሚከሰተው የደም ማነስ መከላከል ይቻላል።ይህንንም የተመጣጠኑ ምግቦችን በመመገብ መከላከል እንችላለን።
በብረት የበለፀጉ ምግቦች በጥቂቱ
ጉበት
ቀይ ስጋ
ዓሣ
ባቄላ፣አተር
ጥቁር ቸኮሌት እና ሌሎች
በቫይታሚን ቢ 12 (vitaminB12) የበለፀጉ ምግቦች በጥቂቱ
ቀይስጋ እና ዓሣ
ዶሮ ፣ እንቁላል
ወተትና ሌሎችም
በፎሊክ አሲድ (folic acid) የበለፀጉ ምግቦች በጥቂቱ
አረንጓዴ ኣትክልት አትክል( ጎመን፣ ሰላጣ)
ጥራጥሬዎች (ባቄላ፣ አተር፣ምስር)
ለውዝ
ፍራፍሬዎች( ብርቱካን፣ሙዝ፣ወይን፣አቮካዶ፣ፓፓያ፣ እንጆሪ )
ቀይ ሽንኩርት እና ሌሎች
በተጨማሪም የሆድ ትላትሎችን የግልና የአካባቢ ንፅናችንን በመጠበቅ መከላከል እንችለላለን።
ከላይ እንደተጠቀሰው እነዚህን ስሜቶችና ምልክቶች ስናስተውል በአፋጣኝ ወደ ወደጤና ተቋም ማምራት ተገቢ ይሆናል።ነገር ግን የመከላከያ ማስታዎሻውን ዘወትር መከተል ለሁላችንም አስፈላጊ እንደሚሆን መገንዘብ ያሻል።
ዶክተር ቤዛ አያሌው
=======================
በፍጥነት እያደገ ያለዉም የቴሌግራም ቻናላችንን ከታች ያለዉን ሊንክ በመጫን ይቀላቀሉ።
👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇
https://t.me/yourhealthethiopia/2061